፴፰ ያን ጊዜም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ሰዎች መጥተው ፤መምህር ! ካንተ ምልክት ልናይ እንወዳለን አሉት ። ፴፱ ጌታ ኢየሱስም መልሶ ከዳተኛዪቱ ፤ ዐመፀኛዪቱ ፤ አመንዝራዪቱ ትውልድ ምልክት ትሻለች ፤ ምልክቱ ግን አይሰጣትም ፤ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ። ፵ ዮናስ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ እንደ ነበረ ፤ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት መዓልት ፣ ሦስት ሌሊት በምድር ልብ ውስጥ ይኖራል ። ፵፩ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ተነሥተው ይህችን ትውልድ ይፋረዱአታል ፤ ያሳፍሩአታል ፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና ፤ እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ ። ፵፪ ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ተነሥታ ከዚች ትውልድ ጋር ትፋረዳለች ፤ ታሳፍራታለች ፤ የሰሎሞንን ጥበብ ትሰማ ዘንድ ከምድር ዳርቻ መጥታለችና ፤ እነሆ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ ።